Tuesday, January 21, 2014

“ፈጣሪ በየትውልዱ የራሱን ድምጽ ያወጣል። የትውልዱን ድምጽ በኔ አድርጐ ማውጣቱን አምናለሁ፡፡” ቴዲ አፍሮ አሁንም ይዘባርቃል::

በምንሊክ በሄኒከን በበደሌ በብዙ ኦሮምያ ወጣቶች በቴዲ አፍሮና በጃዋር መሃከል ሲደረግ የነበረውን ጠብ የሚመስል የቃላት መአት አይቻለሁ:: እነዚህ ምንሊክን የሚቃወሙት እትዮፒያውያን ወንድሞቻችን ያሰቡት ተሳክቶ ተቃውሞዋቸውን በትክክል አሰምተው ሄኒከንን ሃሳቡን አሰርዘዋል:: አርቲስት ቴዲ አፍሮም በትክክል አፍሮ አይቼዋለሁ::
በየማህበራዊ ድህረ ገጾች ክርክሮችና አስተያየቶች በዝተው ለማየት ችያለሁ::  በተለይ የቴዲ አፍሮን ዝናና ክብር ለመጠበቅ ሲለፉ የነበሩ ጋዜጠኞችም ዌብ ሳይቶችም በጣም አሳዝነውኛል:: ፍጹም ለማመን የሚከብድ ስህተት እየሰራ ያለን አንድ ያልተማረ ተራ አዝማሪን ለመከላከልና ለማገዝ የተደረገው ሙከራ ፍጹም የጋዜጠኝነትን ስነምግባር ያልተከተለ እንዲሁም በጥልቅ ሲታይ ውስጡ ባለፉት አስከፊ ዘመናት የነበሩትን ጨፍጫፊዎችን ማምለክ የተያያዘ እንደሆነ ግልጽ ሆኖ ታይቷል::
እነዚህን ጽሁፍ የሚጽፉት ሰዎች የጋዜጠኝነት ሙያቸውን (ካላቸው ነው) በማይረባ ሳንቲምና ፍርፋሪ ሸጠው ከመሳደብና ከመጮህ በስተቀር በሰለጠነ መንገድ በሃሳብ ዙሪያ መከራከር የማይችሉ ያገነኑትን ምንሊክን እንኳን ተሳስቶ ነበር ለማለት የሚያንቃቸው መሆኑን አይቻለሁ:: ይህ ያለንበት ዘመን ደግሞ 2014 እንደሚባልና ይሄ የነሱ ተረት እንደማይሰራ ልነግራቸው ፈለግኩኝ:: ታዲያ በዚህ መሃል የታዘብኩትንና ፍጹም ያልተመቸኝን ነገር ነጥብ በነጥብ አስቀምጣለሁ::
  • ከመጽሄቱ ነው ስህተቱ ወይስ ከቴዲ አፍሮ? ከመጽሄቱ ከሆነ እንዴት ዘፋኙ ያላለውን ቃል እንደ አርእስት ለመጠቀም ፈለገ? ቴዲ አፍሮ ያላለው ከሆነ ለምን ይሄ ሁሉ ሙግት ውስጥ ይገባል በቀጥታ ለምን ያንን የጻፈውን አካል ወይም መጽሄት አይከሰውም?
  • ለመሆኑ የጦርነት ቅዱስ አለው? ቅዱስ ጦርነት የሚለው ይህ ቃል ከራሱ ከቴዲ ካልመጣ እዛው እንቁ መጽሄትን ከሶና አፋጦ እሱ እንዳላለው አሳውቆ ለምን ነገሩን አያበርደውም?
  • ዘፋኙ ባለጌና ስድ ነው እጅግ አላዋቂና ፍጹም አወናባጅ ነው ላለማለት ይሄ ሁሉ የዲያስፖራ ዌብ ሳይት ሙሉ የኦሮሞን ህዝብ ወይም አንድ ጃዋር የሚባልን  ሰው የሚቃወመው ለምንድነው?
  • ቴዲ አፍሮ ፍጹም የማይሳሳት በጣም ድንቅ አእምሮ እንዳለው አድርጋችሁ የምታንቆለጳጵሱት ለምንድነው? ከልጁ የነፍሰገዳይ ማንነትስ እንዴት ተረሳችሁ?
  • እንዲህ ያለ አሳፋሪ አባባል ከሱም ይሁን ከመጽሄቱ አካላት ሲወጣ አንድ ጃዋርንና ብዙ የኦሮሞ ህዝቦችን ስትቃወሙና ስትዘልፉ ለምን ቴዲንና መጽሄቱን ሁለተኛ እንዳይለምዳቸው እንኳን አትገስፁም? እውነት ለመጻፍ አይደል እንዴ የቆማችሁት?
  • በመኪና ሰው ገጭቶ ገድሏል ሲባልም እሱን ከመጠየቅ ይልቅ ወያኔ በፖለቲካ ነው ያሰረው ስትሉ ነበር አሁንም ይሄ ጃዋር ትላላችሁ ለመሆኑ ይታወቃችኋል?
  • በደሌ ይህንን ኮንሰርት የሰረዘው ምንም ጥበቃ ስላላገኘ ለደህንነት ሲባል እንደሆነ እንጂ ፍላጎቱ እንደነበረው ታውቃላችሁ ታድያ እናንተንና ቴዲ አፍሮን የሚያሳስበው ኮንትራቱ ሲዘረዝ የሚገኘው ሳንቲም እንጂ የተከለከለበት ምክንያት አይደለም ማለት ነው?
  • ይሄን ያህል ብር ኮንትራቱ ስለተሰረዘ ይከፈለዋል ስትሉ ምንም የማያሳፍራችሁ ለምንድነው? ይሄ ሁሉ ሺ ሰው ቴዲንና በደሌን አጨናንቆና አስመስክሮ ኮንሰርቱን ሲያሰርዝ እንዴት ከባድ አጀንዳ እንደያዘ ማመን አቃታችሁ? አንድ ተራ አዝማሪ የሚያነሳው ሃሳብ በዚህ ሁሉ ሰው ሲጠላ እንዴት ነው የምታዩት? ነው ወይስ እናንተ ይሄንን ወሬ ስታባዙና ስታናፍሱ የሚከፈላችሁ  ነገር አለ? ምን ይሆን?
  • በአገሩ ከተሞች እንዳይሰራ እየታገደ በህዝቡ እንዲህ አይነት ተቃውሞ እየደረሰበት ቦይኮት እየተደረገ ያለ ዘፋኝን በምን አይነት መለኪያ ነው የምታሞጋግሱት?
  • ፍቅር የፍቅር ጉዞ እያለ የሚያጭበረብር እና የሚያታልል ለራሱ አንዲት መፍትሄ ማምጣት የማይችል አዝማሪ እንዴት በሙሉ የተቃዋሚ ጋዜጠኛ ነኝ ባዩን የዌብ ሳይት ባለቤት ድጋፍ ሊያገኝ ይችላል? ይሄ ምናልባት አርቲስቱና ማናጀር ተብዬው እነዚህን ዌብ ሳይቶች እየደጎሙ በብር እንደያዙት ያስታውቃል ካለዛ እንዲህ አይነት ያፈጠጠ ወሬና አሉባልታ እየተጻፈ አዝማሪውን ለመከላከል ጥረት አይደረግም ነበር::
አጉል መኮፈስ እና አጉል ስለፍቅር ሲባል ከፈጣሪ የተላኩ ዘፋኝ ነኝ ሊል የሞከረበት ተረት ተረቱን እንዳነበብኩ ያስቀመጥኳቸው ደግሞ:
  • ይቅር መባባል ጥሩ ነው ይልና ባሁኑ ሰአት ኦሮሞው ወጣትና አዋቂ የሚጠይቀውን የምንሊክን አምባገነንነት እና የምንሊክ ጨፍጫፊነትን አለማመን ምን የሚሉት እውቀት ነው?
  • ምንሊክ በሰራው መጥፎ ስራ የተቆጣ ህዝብ ምንሊክ እየተባለ እንዲዘፈንና እንዲደለቅ አይፈልግም እንዲህ የሚደርጉትንም ይቃወማል የኔንም ቁስል እየቀሰቀሳችሁ አታስከፉኝ ይላል:: ታድያ በዚህ ዘመን እሺ የኔ ወንድም የኔ ኦሮሞው አካሌ ብሎ እንደመተው ለምን ጭራሽ ነገሩን ከፍቅር ማጣት ጋር ሊያይዘው ይሞክራል?
  • ፍቅር እያሉ እንዲህ ያፈጠጠ የወንበዴ እና የቁጭ በሉ ስራ መስራት በህግ እንደነ ታምራት ገለታ እንደሚያስቀጣ አታውቁም እንዴ? ቴዲ አፍሮ የሚባል ዘባራቂ አዝማሪ በሚችለው የዘፈን ሙያው እንዲ አይነት ቀውስ ለመፍጠር በዚህ መሃል በሚገኘው ትርምስ እና አጋጣሚ እኔ ከፈጣሪ የተላኩኝ ነቢይ ነኝ ለፍቅር የመጣሁ መሲህ እያለ ሳንቲምና ዝና ማግኘት የሚፈልግ የድሮ ዘመን እርድናውን በዚህ ዘመን ሊሞክር የሚፈልግ ድንቁርና የተጠናወተው ተራ አዝማሪ መሆኑን ካልነገርነው ማን ሊነግረው ነው?
  • ምንሊክ ጨፍጫፊ ስለነበር አልወደውም የሚል ሰው እንዴት ነው ችግሩ በፍቅር የሚፈታው? ምንሊክ እያሉ በመዝፈን? ወይስ የወገኔን ቁስል አልቀሰቅስም ብሎ ምንሊክን እጅግ ባለማወደስ? ቴዲ ፍቅር እያሉ ፉገራ በጣም ተመችቶታል ምክንያቱም ፍቅር የሚለው ቃል እግዚያብሄር የሚለውን ትርጉም ስለሚያሰጥ ግን ፍቅርን የሚያቅ ቢሆን ድሮም ሰው ገጭቶ አያመልጥም አሁንም ወንጀለኛና ጨፍጫፊን አያሞጋግስም ነበር::
  • ፈጣሪ ለዚህ ትውልድ በማሰብ ለፍቅር ብሎ ነው የላከኝ ብሎ በዚህ ዘመን ሊፎግር የፈለገን ዘፋኝ ማን ጸጥ ይለዋል? እነ ጃዋር አዲሱ ትውልድ መሆናቸውን ቴዲ ረሳው እንዴ?
  • “ህይወት የሚቀጥለው፣ ካለው ነገር ላይ በመነሳት ነው፡፡” የተምታታበትና ግራ የተጋባው ቴዲ አፍሮ የሚያወራው በራሱ በጣም ይቃረናል—— የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ ደሞ ይለናል::
  • “ፈጣሪ በየትውልዱ የራሱን ድምጽ ያወጣል። የትውልዱን ድምጽ በኔ አድርጐ ማውጣቱን አምናለሁ፡፡” ብሎ ሲዳፈር በጋዜጠኞች የሚታገዘው 2006ዓ.ም መሆኑን ረስተውታል እንዴ?
  • አፍሪካን ሊወክል በህብረት ዘፈን ሰራ ተብሎ ዜናውን ለማረሳሳት ያየነው ዘፈን ላይ እንኳን ሊዘፍን ምንም የአጃቢ ቦታም እንዳላገኘ ለማየት ችያለሁ:: ለብቻው ነጥዬ ልሰማው ብፈልግም አንዲት ቃል አጥቼበታለሁ እንኳንስ ሊያኮራኝ ይቅርና ተራ ዘፋኝ መስሎ ሳየው አሳዝኖኛል ምናልባት ሌላ ቦታ እያወናበዱ መዝፈን እንደማይቻል አያውቅ ይሆናል::
ጋዜጠኞችም ከሰው ጥያቄዎችን ለምን እንደማትጠይቁት በጣም አስተውለናል ፊት ለፊት ጠይቁት እና መልሶችን ከአንደበቱ እንስማው ዛሬ ይዘባርቃል ነገ ደግሞ እኔ አላልኩም ይላል:: ዛሬ ሰው ይገጫል ነገ ደሞ መንግስት አሰረኝ ይላል:: እንዲ አይነት አጭበርባሪ ነገ ደግሞ ነቢይ በአገሩ አይከበርም እንደሚል አልጠራጠርም::
ሰላም ሁኑ በፍቅር ስም ከሚያደናቁሩ ይጠብቃችሁ::
ቴዲ አፍሮ ነቢይ ነኝ ስሙኝ ሊል የፈለገበትን ቃለ ምልልስ አንብቡት  ነገ ደግሞ አላልኩም ማለቱ አይቀርም:: ቂቂቂቂቂቂቂቂቂቂቂቂ….
በሳምንቱ መጨረሻ ቴዲ አፍሮ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ቆይታ ነበረው፡፡ በሁለት ክፍል የተደረገውን ቃለ-ምልልስ የመጀመሪያ ክፍል እነሆ ፡)
“ከወረስነው ቂም ይልቅ የምናወርሰው ፍቅር ይበልጣል”
“ፈጣሪ በየትውልዱ የራሱን ድምጽ ያወጣል”
“ፍቅር ያሸንፋል– የኔ ሳይሆን የትውልድ ድምጽ ነው”
“እዳ አለ የምንል ከሆነም፤ እዳ የሚከፈለውና የሚሸፈነው በፍቅር ብቻ ነው
“ከታሪክ ከወረስነው ቂም ይልቅ የምናወርሰው ፍቅር ይበልጣል”
የፍቅር ጉዞ ከሚለው ሃሳብ እንጀምር፡፡ መነሻው ምንድነው?
“አቦጊዳ ብዬ፣ ፊደል “ሀ”ን ቆጥሬ፤
የፍቅርን ትርጉም ለልቤ አስተምሬ፣
ይዤሽ በአኮፋዳ እንደቆሎ ተማሪ፣
አቦጊዳ ልበል የፍቅር ጀማሪ…”
እንዲህ ነው የኔ የዘፈን ህይወት የሚጀምረው። አሁን የፍቅር ጉዞ ላይ ደርሷል፡፡ ሁላችንም፣ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ውስጥ እናልፋለን። ብዙ ቅሬታና ብዙ ደስታ፣ ብዙ ትክክል የሆኑ ነገሮችና ብዙ ትክክል ያልሆኑ ነገሮች አሉበት – ያለፍንበት ታሪክ፡፡ ትልቁ ነጥብ፣ ካለፍንበት ታሪክ ተነስተን ለሚቀጥለው ጊዜ ምን እናድርግ የሚለው ነው፡፡ ያዘንበትን ነገር በይቅርታ ሰርዘን፣ የወደድነውን ነገር ደግሞ አሳድገን ለመጓዝ፣ ትልቁ መድሃኒት ፍቅር ነው፡፡ ይቅር ተባብሎ የቀድሞ ስህተቶችን ለማስተካከልና በህብረት ተጠራርቶ የቀድሞ ትክክለኛ ነገሮችን ለማሳደግ፣ ፍቅር ያስፈልጋል፡፡ አቡጊዳ ብለን ነው ፍቅርን የምንጀምረው፡፡ “ዳህላክ” ላይም፣ ለልጆቻችን ቂምን አናውርስ ብለናል፡፡ “ካስተማርሽው ፍቅርን በጊዜ፣ አይሻለሁ ወይ ባሱ ጊዜ…” ኢትዮጵያና ኤርትራ ተራርቀው የተፈጠረው ግጭት የሩቅ ጊዜ ታሪክ አይደለም። የብዙዎችን ህይወት በቀጠፈው ግጭት፣ ብዙ የተበተነ ቤተሰብ፣ የደማ ስሜት አለ፡፡ ይሄ ቁስል ዘላለም እንደመረቀዘ መቀጠል አለበት? መዳን መፈወስ የለብንም? ይቅር መባባልን ነው በ“ያስተሰርያል” የዘፈንነው፡፡ ለምንወልዳቸው ልጆች፤ ለምንፈጥራቸው አዲስ ትውልዶች የምናወርሰው ቂምን ከሆነ፣ ያለፈው መቁሰል ሳይበቃ ለወደፊትም ሌላ አደጋ እንዲፈጠር እየተባበርን ነው ማለት ነው፡፡ የሚሻለው መፍትሔ፣ እኛ የወረስነው አለመግባባት ካለ፣ በቂም ሰበብ የተቋሰልነው ነገር ካለ፣ የአዲሱን ትውልድ ህይወት እንዳያውክ፣ እኛ ጋ መቆም አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
የዘመናችን ፈተናዎች ሳያንሱ፣ የቅርብ ጊዜ የቂም ታሪክንም እየተሸከመን፣ ከዚያም አልፎ የሩቅ ጊዜ የቅሬታ ታሪኩንም እየቆሰቆስን ቂምን የምናወርስ ከሆነ፣ ለማናችንም ሕይወት የማይጠቅም፣ የልጆቻችንንም ተስፋ የሚያጨልም አደጋ እየፈጠርን እናልፋለን፡፡ ቂምን መሻር፣ ቁስልን መፈወስ፤ ከዚያም አልፎ ለሁላችንም የሚበጅና የተስፋ ብርሃንን የሚያደምቅ ነገር መስራት የምንችለው በፍቅር ነው፡፡ ከ “አቡጊዳ” እስከ “ያስተሰርያል”፣ “ዳህላክ”፣ ቀላል ይሆናል”…እና ሌሎች ዘፈኖች ይህንን መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ግን ልዩ አዋቂ ስለሆንኩ ወይም ልዩ ሃይል ስላለኝ አይደለም፡፡ በፈጣሪ ሃይል ነው። ፈጣሪ በየትውልዱ የራሱን ድምጽ ያወጣል። የትውልዱን ድምጽ በኔ አድርጐ ማውጣቱን አምናለሁ፡፡ አሁን፣ ቅን እና ጥሩ ትውልድ አለ፡፡ የዚህ ቅን ትውልድ ድምጽ የፍቅር ድምጽ ነው። ግራ የሚያጋቡ፣ የሚያስጨንቁና የተተበተቡ ችግሮች ሁሉ በፍቅር ይፈታሉ፡፡ ከቂም፣ ከቁስል በፍቅር እንዳን፣ ፍቅር ያሸንፋል የሚለው መልዕክት የኔ ሳይሆን የትውልድ ድምጽ ነው፡፡ ይህ ቅን ትውልድ ተቀራርቦ፣ ተሰባስቦ አንድ ላይ የፍቅር ድምፁን የሚያስተጋባበት እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ነው የፍቅር ጉዞ፡፡
በፖለቲካም ሆነ በሌላ ምክንያት፣ በተለያየ ችግርና አለመግባባት በአገራችን ለተከሰተው ቂምና ቁርሾም፣ እዚህ አገር ቤትም ሆነ በየአገሩ ተበታትነው የሚገኙ ወገኖቻችን፣ ቢያንስ ለልጆቻቸው ሲሉ ይቅር መባባልን እንዲቀበሉ ለመጋበዝ፤ የአዲሱ ትውልድ ስሜትም ይሄ እንደሆነ የሚገልፁ ዝግጅቶችን ለማቅረብ ነበር ያቀድነው፡፡ ዝግጅቱን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በስፋት ለማዳረስ ነው፤ በሄኒከን ከሚተዳደረው በደሌ ቢራ ጋር ተነጋግረን ውል የተፈራረምነው፡፡ በተፈራረምንበት እለት እንደተገለፀውም፤ የቋንቋና የብሔር ስብጥር ውስጥ ህብረትና አንድነታችንን የሚያጠናክር፣ ቂም እንዳንወርስና መልካም መንፈስን ለመጋራት አንድ ላይ የሚጮህ የፍቅር አላማ ያለው ዝግጅት ነው፡፡
ግን፣ የኢትዮጵያ ታሪክም ሆነ የኢትዮጵያውያን ሕይወት አንተ እንደምትለው፣ በፍቅርና ሰላም ብቻ የተሞላ ሳይሆን፣ በቂምና በግጭትም የተበረዘ ነው፡፡ አይደለም?
ምን ጥርጥር አለው! ያሉና የነበሩ ነገሮች ናቸው፡፡ የህይወት እና የደስታ ውድነት ትርጉም የሚኖረው ከሞትና ከሀዘን ጋር ነው፡፡ የፍቅር ውበት የሚጐላው፣ ከጥላቻ ጋር ሲነፃፀር ነው። ነገር ግን ያሳዘኑን ነገሮች ላይ ብቻ ስናተኩር፣ አዲሱንና የወደፊቱን ትውልድ ያውካል፡፡ እዳ አለ የምንል ከሆነም፤ እዳ የሚከፈለውና የሚሸፈነው በፍቅር ብቻ ነው፡፡ ፍቅር መድሃኒት ነው፡፡ የነገር ሁሉ መጀመሪያና መጨረሻ ነው፡፡ ሁላችንም ህፃናትን ማቀፍና መሳም የምንወደው ለምንድነው? ገና ሲወለዱ፣ ገና ከመነሻው ሲፈጠሩ ፍፁም ፍቅር ስለሆኑ ነው፡፡ ያ የፍቅር ሃይል ነው የሚስበን፡፡ ህፃኑም እናቱ ጉያ ውስጥ የሚገባው በፍቅር ሃይል ነው፡፡ እንኳን ሰውን የመሰለ ክቡር ፍጥረት ይቅርና አውሬ የምንላቸው እንስሳት ውስጥም የምናየው የተፈጥሮ ሃይል ነው፤ ፍቅር፡፡ ነገር ግን በኑሮ ውስጥ በብዙ ውጣ ውረድ፣ ብዙ ቅሬታዎችና እንከኖች ስለሚያጋጥሙን ፍቅራችንን ሊበርዙብን ወይም ውስጣችንን መርዘው የውስጥ ህመም ሊሆኑብን ይችላሉ፡፡ ባዘንበትና በተቀየምንበት ነገር ላይ ቆመን ተውጠን ስንቀር በሽታ ይሆኑብናል፡፡ ለቅያሜ እልባት እየሰጠንና እየሰረዝን ካልሄድን፣ ይባስ ብለን ለልጅ ልጅ እያወረስን ከቀጠልን፣ በማህበረሰብ ደረጃ እንደዝገት ውስጣችንን እየበላ ይጨርሰናል ወይም እንደተዳፈነ እሳት በሆነ አቅጣጫ ተግለብልቦ ያቃጥለናል፡፡
እና ምን ይሻለናል ብለን ስናስብ፣ በቀድሞ ዘመን ወይም ባለፍንበት ጊዜ የተፈፀሙ መልካም ነገሮችን ወይም ስህተቶችን እንዳልነበሩ ማድረግ አንችልም። ወደኋላ ተመልሰን በህይወት የሌሉ ሰዎችን መሸለም ወይም እዳ ማስከፈል አንችልም፡፡ እነሱ በዘመናቸው አልፈዋል፡፡ ነገሩ ያለው የዛሬ ነዋሪዎች ላይ ነው፡፡ በቀድሞ ሰዎች ታሪክ የምንደሰትበትና የምናዝንበት፣ ትክክል የሆኑና የተሳሳቱ ስራዎች፣ የወደድነውና የተቀየምንበት ነገር ይኖራል፡፡ ቀጥለው የመጡ ትውልዶች የትኛውን ስሜት መያዝ፣ የትኛውን ስሜት ማውረስ አለባቸው? እኛስ የትኛውን ወርሰን የትኛውን ማሳደግ አለብን? ቅሬታና ቂምን ይዘው ያወርሱናል ወይስ ፍቅርንና መዋደድን? ቅያሜና ቂም ብንወርስ ምን ይበጀናል? ወደ ኋላ ተመልሰን እዳ ማስከፈል አንችል? ህይወት የሚቀጥለው፣ ካለው ነገር ላይ በመነሳት ነው፡፡ ስህተቶችን ትተን፣ ትክክል የሆኑትን ይዘን፣ ያን እያሳደግን ነው መቀጠል ያለብን፡፡ ታላላቆቻችን በተለያዩ አለመግባባቶች ውስጥ ያልፋሉ፡፡ አለመግባባትና ቅሬታ ባይፈጠር መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ቢያንስ፣ የታላላቆችን አለመግባባት ወደ አዲሱ ትውልድ እንዳይሻገርና መጪውን ጉዞ እንዳያውክብን፣ ታላላቆቻችን ስለ አዲሱ ትውልድና ስለመጪው ትውልድ መጨነቅ ያስፈልጋቸዋል ብዬ አስባለሁ። ፍቅር ያሸንፋል የሚለው የታናናሾች የአዲሱ ትውልድ ድምጽም ጐልቶ መሰማት እንዳለበት አምናለሁ፡፡ የፍቅር ጉዞ የዚህ የአዲሱ ትውልድ መንፈስ ነው፡፡
የፍቅር ጉዞ ዝግጅት ከበደሌ ቢራ ጋር ተፈራርመህ በሳምንቱ ነው ውዝግብ የተፈጠረው። እንዴት ነበር የሰማኸው?
ከጊዜ በኋላ ነው የሰማሁት፡፡ አንደኛ በድሬዳዋ አንድ ተብሎ የሚጀመረው ጉዞ፣ ትልቅ የፍቅር መልዕክት የያዘ ስለሆነ፣ ያልተበታተነ ትኩረት ይፈለጋል፡፡ ከዚህ ውጭ ባለው ጊዜ ደግሞ፣ በሚቀጥለው መስከረም ወይም ብዙ ሳይቆይ አዲስ አልበም ለማድረስ የጀመርኩት ስራ አለ፡፡ ሁለቱም ቀናተኛ ስራዎች ናቸው፡፡ አእምሮህ ሌላ ነገር እንዲያስተናግድ አይፈቅዱልህም፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ባልደረቦቼ በኢንተርኔት በተፈጠረው ውዝግብ ዙሪያ ሊያናግሩኝ ሲሞክሩ ስራ ላይ ሆኜ ብዙም ፈቃደኛ አልነበርኩም፡፡ ሲደጋገም ግን ሰማሁ፡፡ ማኔጀሬ (ዘካሪያስ) ተጨንቆ ነው የነገረኝ። ከሥራ አስኪያጅ አንፃር ሆነህ ስታየው መጨነቁ አይገርምም፡፡ ግን ተረጋግተን ነው የተነጋገርነው፡፡
አልተረበሻችሁም?
ነገሩን አቅልለን አላየነውም፡፡ የፍቅር ጉዞ ትልቅ ዝግጅት ነው፡፡ ነገር ግን፣ በብዙ ወጣ ገባ መንገድ ከማለፍ እና ብዙ ውጣ ውረድ ከማየት የተነሳ፣ ችግሮችን ማስተናገድ ትለማመዳለህ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የፍቅር መልእክት፣ በቴዎድሮስ ካሳሁን የተፈጠረ ሃሳብ አይደለም፡፡ የነበረ ያለና የሚኖር የእግዚአብሔር ሃሳብ ነው፡፡ ያንተ ድርሻ ያ ሃሳብ ሲሰጥህ መቀበል ነው እንጂ፤ አንተ ከምትጨነቀው በላይ ከምንም አስበልጦ፣ ፈጣሪ ስለ አላማውና ስለሃሳቡ፣ ስለ እኛ እና ስለትውልዱ ስለሚጨነቅ፣ ብዙ አልተሸበርንም፡፡ ሁሉንም ነገር ለበጐ ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
“ጥቁር ሰው” በሚለው ዘፈንህ በአድዋ ጦርነት ዙሪያ ምኒልክንና ሌሎች የታሪክ ሰዎችን በማንሳት ዘፍነሃል፡፡ የምኒልክ ታሪክ ላይ ያለህን አስተሳሰብ በቅርቡ ቃለ ምልልስ አድርገህ በመጽሔት ታትሟል፡፡ ከዚህ ቃለ ምልልስ ጋር ተያይዞ ነው የምኒልክ ጦርነት ቅዱስ ነው የሚል አወዛጋቢው አባባል የተሰራጨው፡፡
በመጽሔት ታትሞ በወጣው ቃለምልልስ ላይ፣ እንደዚያ አይነት አባባል የለም፡፡ “አካሄዱን ያየ አመጣጡን ያውቃል” በሚል ርዕስ በእንቁ መጽሔት ታትሞ የወጣውን ቃለምልልስ ማየት ይቻላል፡፡ በምኒልክ መቶኛ የሙት ዓመት መነሻነት የተደረገ ቃለምልልስ ነው፡፡ በዚህ ቃለምልልስ ውስጥ ማንንም የሚያስቀይም አባባል የለበትም፡፡ ነገር ግን በኢንተርኔት ሲሰራጭ የኔ ያልሆነ አባባል ታክሎበት የተከፉ ሰዎች እንዳሉ ስሰማ፣ የተሳሳተውን መረጃ ለማስተካከል ምላሽ ሰጥተናል፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን፣ የመጽሔቱ አዘጋጅም አወዛጋቢው አባባል እኔ የተናገርኩት እንዳልሆነ፣ በመጽሔቱ ህትመት ውስጥም እንዳልነበረ አስረድቷል፡፡ ነገር ግን ውዝግቡ በዚህ አልተቋጨም፡፡ ለምን የፍቅር ጉዞን የሚያስተጓጉል ነገር ተፈጠረ አልልም፡፡ እዚህ ምድር ከተገለጡትም ሆነ ካልተገለጡት ሃይሎች ሁሉ የሚልቀው ፍቅር ነው፡፡ ክብደቱም የዚያኑ ያህል ነው፡፡ ስለዚህ የፍቅር ጉዞ ብለህ ስትነሳ፣ ያለ እክል እና ያለ ችግር ትደርሳለህ ማለት አይደለም፡፡ እንኳን ትልቁና ከባዱ ጉዞ ላይ ይቅርና፣ እንደ ቀላል የምናያቸው ጉዞዎች ላይም፣ ወደ ናዝሬት ወይም ወደ አዋሳ ለመሄድ ስትነሳ እንኳ፣ በመኪኖች መጨናነቅ ጉዞህ ሊጓተት ይችላል። ጐማ ቢተነፍስ ወይም ሞተር ቢግል፣ ጐማ ለመቀየርና የራዲያተር ውሃ ለመለወጥ መቆምህ አይቀርም፡፡ ከሁሉም የከበደው የፍቅር ጉዞ ላይማ፣ ለምን ፈተና ይፈጠራል ማለት አይቻልም። ከምንም በላይ ይቅር መባባልን የሚያበዛ የእርቅ መንፈስን ይዘህ ስትጓዝ፣ እንዲያውም ከተቻለ ታላላቆችህም እንዲግባቡልህና መግባባትን እንዲያወርሱ ስትጮህ፣ በዚህ ምክንያት ካንተ ጋር የማይግባባ ነገር ሲፈጠር፣ ነገሩን ንቀህ የምታልፈው አይሆንም፡፡ ምንም እንኳ፣ በተሳሳተ መረጃ ምክንያት የተፈጠረ ቅሬታ ቢሆንም፣ አንተም በተራህ የቅሬታ ባለቤት መሆን የለብህም፡፡ ፍቅር ሁሉንም ያቅፋል፡፡ በተሳሳተ መረጃ የተነሳ ያልወደደህንም ሰው ማቀፍ አለበት።

No comments:

Post a Comment