ቦሩ በራቃ | July 29,2014
የሰው ለ ሰውን ድራማ እስከ መጨረሻው (ክፍል 140) ድረስ ተከታተልኩት። እንደ ብዙዎቹ ሁሉ እኔም የኣቶ እስናቀ ኣሸብርን መጨረሻ ለማየት በጥቂቱም ቢሆን መጉዋጉዋቴ ኣልቀረም። በድራማው የትወና ድር ሁሉም ቅርንጫፎች በስተጀርባ ብቸኛውና ቀንደኛው ጠላት ተደርጎ የተፈረጀውን እስናቀ ኣሸብር! ይህ ድራማ ከተጀመረበት ወቅት ኣንስቶ የኣስናቀን የትወና ሚናና ብቃት የተከታተሉት ኣንዳንድ ወገኖች ድራማውን በፖለቲካ መነጽር ሲቃኙት ከመለስ ዜናዊ ኣምባገነንነትና ብልጣብልጥነት ጋር ያገናኙታል። ለኔ ግን ይህ ኣይዋጥም። በፖለቲካ መነጽር ድራማውን እንቃኘው ከተባለ እኔ የኣስናቀን ሚና የማስቀምጠው በሌላ መልኩ ነው። እስናቀ በድራማው ውስጥ የተሳለው ከኣምባገነንነቱ ይልቅ በስግብግብነቱ ነው። በብልጣብልጥነቱም ሳይሆን ራሱን ብልጥ ኣድርጎ የሚያስብ ነገር ግን በውስጣዊ ማንነቱ ቂል ተደርጎ ነው። በኣጭሩ ይህ ኣስናቀ የተባለው ግለሰብ ሞኝና ስግብግብ ነው።
ይህ ደግሞ ብዙዎቹ ኣቢሲኒያዊ ፖለቲከኞች የኦሮሞን ብሄረተኝነት የሚተረጉሙበት የተለመደ ምስል ነው። ኦሮሞዎች ኦሮምያ የኦሮሞ ናት በማለታቸው ብቻ በኣቢሲኒያዊያኑ ፖለቲከኞች ዘንድ ስግብግብ ተደርገው ይታያሉ። ኦሮሞ ምንም በብዙህነቱና ኢኮኖሚያዊ ኣቅሙ ልቆ የወጣ ህዝብ ቢሆንም እነርሱ ዘንድ ሁሌም እንደ ቂል ይቆጠራል። ኦሮሞ በጭንቅላቱ ብስለት ሳይሆን በጡንቻው ኣቅም የሚያስብ ተደርጎ ይተረጎማል። ተማረ ኣልተማረ ኦሮሞ ስልጡን ሊሆን ኣይችልም እያሉም የሚያንቁዋሽሹትና የሚሳለቁበት ቁጥራቸው ቀላል ኣይደለም።
ሰው ለ ሰው ድራማ ውስጥ ለኣስናቀ ኣሸብር (ኣበበ ባልቻ) የተሰጠው የትወና ሚናም ከዚህ የፖለቲካችን እውነታ ጋር የሚመሳሰልበት መልኩ ብዙ ነው። ገና ሲጀመር ኣስናቀ ኣሸብር ‘እሸባሪ’ ተደርጎ ነው የተሳለው። የኦሮሞ ህዝብ ብሄርተኝነትም ከኦነግ ጋር ተያይዞ በእሸባሪነት እንደሚፈረጅ ልብ ይሏል። የኣስናቀ እሸብርን ባህሪይ ተላብሶ የሚጫወተው ተዋናዩ ኣበበ ባልቻ ራሱ በድራማው ውስጥ እስከ መጨረሻው ድረስ ሚናቸውን ይዘው ከዘለቁት ተዋናዮች መካከል ብቸኛው ኦሮሞ ነው። የጋሽ ኣስኒ ብሶት የሚጀምረው ከኣንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ህይወቱ ነው። የድሃ ቤተሰብ ልጅ ነበረ። ሁሌም በትምህርት ቤት ጉዋደኞቹ መሃል ብቸኛው የበይ ተመልካች ነበረ። በልጅነቱ ከነ መስፍን ጋር ሚኒስትሪ ተፈትኖ ፈተና ወደቀ። እነ መስፍን ፈተና ኣለፉ። ፈተና በወደቀው ኣስናቀ ላይም ተሳለቁበት። ኣስናቀ በወቅቱ የሁሉም ልጆች መሳለቂያ መሆኑ በእጅጉ ኣማርሮት ነበር። ነገር ግን በድራማው ኣብዛኛው ክፍሎች ውስጥ ደጋግሞ ስሙን ሲያነሳው የሰማነውና የኣፋን ኦሮሞ ተረቶችን ልቅም ኣድርጎ ያስተማረው ኣሳዳጊ ኣጎቱ ነበር በኣጭር ምክር ያረጋጋው።
ኣስናቀ በጨቅላ እድሜው ኣንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ያሳለፈው ኣሳዛኝ ገጠመኝ ኣብዛኞቹ የኦሮሞ ልጆች በልጅነት የትምህርት ዘመናቸው በቀደመው ዘመን ካሳለፉት ጣጣ ጋር ይመሳሰላል። ትምህርት ቤት ውስጥ ልክ እንደ ኣስናቀ መነጠል፣ መዘለፍና መሳለቂያ መሆን ነበረ እድላቸው። ኣስናቀ እያደገ ሲሄድ የኣውሬነት ባህሪይ እንዲላበስ ጫና ያደረገበትም ይሄው ያኔ የተሳለቁበትንና ለብቻው የነጠሉትን የልጅነት ኣብሮ ኣደጎቹን የመበቀል ምኞት መሆኑ በተደጋጋሚ በኣስናቀ ኣንደበት ተነግሮናል።
በዛሬው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሃበሾቹ ዘንድ በሰይጣናዊነት እየተፈረጀ ያለው የኦሮሞ ብሀረተኝነት ፖለቲካ (Oromo nationalism) ነው። ሰው ለ ሰው ድራማ ውስጥም ትልቁ ሰይጣን ተደርጎ የተሳለው ኣስናቀ ኣሸብር ነው። በዛሬው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሃበሾቹ ነጥለው ለመምታት እያደቡበት ያለው ብቸኛው የፖለቲካ ሃይል ቢኖር የኦሮሞ ብሄረተኝነት ነው። በሰው ለ ሰው ድራማ ኣብዛኛው የትረካ ፍሰት (story flow) ውስጥም ኣስናቀ የሁሉም ጠላትና ‘ጸረ ሰላም’ ተደርጎ ነው የተሳለው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ የረጅም ዘመን ታሪክ ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ ብሄረተኝነት ንቅናቄ ፍትሃዊነቱ የታወቀ ቢሆንም በኣገር ክህደትነት ተፈርጆ ጭራቃዊ ምስል እየተሰጠው በሁሉም ዘንድ እንዲወገዝ ያልተፈነቀለ ድንጋይ የለም። በዚህ ድራማ ውስጥ ለኣስናቀ የተሰጠው ሚናም ኣጉል የተንዛዛና እጅግ የተጋነነ ርህራሄ ብስነት ነው። ድራማውን የተከታተለ ሁሉ ኣስናቀን በጨካኝነቱ እንዲጠላውና እንዲረግመው ተደርጎ ነው የተሳለው። በኦነግና በኦሮሞ ብሄረተኝነት ላይ ሲካሄድ ከኖረውና ዛሬም ሳይቁዋረጥ ከቀጠለው ኣደገኛ ስም የማጥቆር ፕሮፓጋንዳ ጋር ይመሳሰላል። በፖለቲካው ህይወታችን ኦሮሞን ከሁሉም ጋር እያናቆሩት የተቀሩት ህዝቦች ጠላት ኣድርጎ ለማቅረብ የሚደረገው ሙከራ በሰው ለ ሰው ድራማ ውስጥ ኣስናቀን የሁሉም ብቸኛና ኣውራ ጠላት ኣድርጎ ከመሳሉ ጥረት ጋር በጣሙን ይመሳሰላል። ይህ ደግሞ የኣስናቀ ኣሸብርን ባህሪይ ተላብሶ ከሚሰራው ከኣበበ ባልቻ ኦሮሞነት ጋር ሲደመር ኣስናቀ ራሱ ኦሮሞ የመሆኑን ፍንጭ በድራማው መሃል በሚናገራቸው ተረቶች ኣማካኝነት ስለነገረን ነገርዮው ከኣገሪቷ ፖለቲካ ጋር እንዲመሳሰል ሆን ተብሎ የተደከመበት ኣስመስሎታል።
በድራማው ውስጥ የኣስናቀ ፍጻሜ ምን እንደሚመስል ቃኝተን ይችን ማስታወሻ እናጠቃልላለን። እኔ በድራማው ፍጻሜ ላይ የጠበቅሁት ኣስናቀ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብና ምናልባትም የሞት ፍርድ እንደሚፈረድበት ነበር። ነገር ግን ማንንም ሳይጎዳ በፖሊሶቹ ቁጥጥር ስር መዋል ሲችል ጥይት ተተኮሰበት። የድራማው ደራሲና ዳይሬክተሮች ኣስናቀን ‘ኣስተማሪ’ በሆነ መልኩ በህጋዊ መንገድ ሊቀጡት ኣልፈለጉም። ትእግስት ኣጡ። ‘ደማቸው ፈላ’ መሰለኝ ኣላስቻላቸውም። ያም ኣልበቃቸው። በጥይት ተምትቶ ከፎቁ ማማ ላይ ሊወድቅ ሲል ኢንስፔክተሩ ኣንድ እግሩን ይዞ ሊያስቀረው የሚሞክር መስሎ ታይቶ ነበር። እዚያ ጋር ኣስናቀና ኢኒስፔክተር ፍሬዘር ኣንድ ትልቅ ፖለቲካዊ ትርጉም ሊኖረው የሚችል ዳያሎግ የሚያደርጉ መስሎኝ ጠብቄ ነበር። ግን እድሉን ኣመከኑት የድራማው ዳይረክተሮች። ኢኒስፔክተሩ ጨክኖበት ኣስናቀን ቁልቁል ለቀቀው። የኣብራኩ ክፋይ የሆነው ልጁና ሚስቱ ከድተውት ከባህር እንደወጣ ኣሳ ብቻውን የቀረው ከርታታው ኣስናቀም የጣር ድምጽ እያሰማ ቁልቁል ተለቆ በሚዘገንን መልኩ ይቺን ኣለም ተሰናበተ። የኣስናቀ ሞት ለድራማውም ፍጻሜ ማበጀቱ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ የድራማው ኣከርካሪና ዋነኛው ባለ ሴራ ኣስናቀ መሆኑን የሚያስመሰክር ነው።
ሰው ለ ሰው ድራማ በስነ ጥበባዊ ብቃቱ ሲመዘን ብዙም እንከን የሚወጣለት ባይሆንም መነሻ ሃሳቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከምናውቀው የፖለቲካ ሴራና ጥላቻ ጋር የመመሳሰሉ ነገር ጥያቄ የሚያጭር ይመስለኛል። ድራማውን በጥሞና የተከታተሉ ወገኖች ለድራማው መነሻ ሃሳብ ጸናሽ ወይም ወይም ለደራሲው በርካታ ፈታኝ ጥያቄዎችን እንዲያቀርቡ የሚገፋፋ ሳይሆን ኣይቀርም። ኣስናቀ እሸብርን በኣንዳንድ የድራማው ክፍሎች ውስጥ በብቸኛ ኦሮሞነት ስለው በኣፋን ኦሮሞ እያስተረቱት ሚናውንም የቀንደኛ ሰይጣናዊነት ባህሪይ ማላበስ ሳያንሳቸው ፍጻሜውን የህግ ሰዎች በተገኙበት ሆን ብለው ህገ ወጥና ሰቅጣጭ ኣድርጎ ማጠናቅቅን መምረጣቸው በእጅጉ ኣስገርሞኛል፣ ኣሳፍሮኛልም። በዚህ ሳቢያ ለሚቀርብላቸው ፖለቲካ ነክ ጥያቄዎች ምላሻቸው ምን እንደሚሆን ኣይገባኝም። የተለያዩ ኣገራዊ ጽንሰ ሃሳቦችን የሚያንሸራሽር እንዲህ ያለ የኪነ ጥበብ ስራ ይቅርና ተራ ስፖርት ሁሉ ደንበኛ የፖለቲካ መስክ በሆነበት ኣገር ይህን መሰሉን በኣንድ የታወቀ ማንነት ባለው ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ኪነ ጥበባዊ ጦር የመስበቁ ውጤት ኣደገኛነት ካሁኑ ያስፈራኛል።
እንዲህም ሆኖ ግን በመጨረሻ ከድራማው ተዋናዮች መካከል ለነ ኣስናቀ፣ ሶስና፣ ማህሌት፣ ኢኒስፔክተር ፍሬዘር፣ ቢኒያም፣ ሞገስና ለነመዲ እናት የጥበብ ብቃት ያለኝን ኣድናቆት ሳልገልጽ ኣላልፍም። በተለይም ኣስናቀን በሰው ለ ሰው ድራማ ደረጃ ብቻ ሳይሆን የኣገሪቷ የትወና ኣይኮን ብየዋለሁ።
ቸር እንሰንብት!
ቦሩ በራቃ
No comments:
Post a Comment