Thursday, December 12, 2013

ወቅቱ የኦሮሞ ህዝብ በይበልጥ ታጥቆ ራሱን የሚከላከልበት እንጂ ባህላዊ ትጥቁ ሳይቀር በጠላት የሚፈታበት ወቅት ሊሆን ኣይገባም

abo

OLF Info Desk

የወያኔ መንግስት የኦሮሞን ህዝብ ዋነኛ የጥቃት ኢላማው በማድረግ ካለፉት ስርኣቶች ሁሉ የከፋ ስለመሆኑ ኣያጠያይቅም። በተቻለለት መንገድ ሁሉ ይህን ህዝብ በማዋረድና በማዳከም ላይ ሲተጋ ይታያል። ወያኔ ለሁለት ኣበይት ጥቅሞች ሲል ከኦሮሞ ህዝብ ጫንቃ ላይ ኣለመውረድን ኣሻፈረኝ ብሏል። የመጀመሪያው የኢኮኖሚ ጥቅም ነው። የኦሮምያን ሃብት ዘርፎ ጡንቻውን እያፈረጠመበት የኣገዛዝ እድሜውን ያራዝምበታል። የወደፊት ኣገሩንም ይገነባበታል። ሁለተኛው የፖለቲካ ጥቅም ነው። ኣለምን በሚያታልልበት የውሸት ዴሞክራሲያዊው ስርኣት ውስጥ የዚህን ብዙሃን ህዝብ ድምጽ በሃይል እየነጠቀ በኣገሪቷ መሰረተ-ሰፊ ድጋፍ ያለው መንግስት ራሱን ኣስመስሎ ኣውጇል። በይስሙላ ፓርላማው ውስጥ በኢህኣዴግ ኣባልነት ብዙሃኑን ወንበር ይዞ ሁሌም ስርኣቱን ከሽንፈት ኣደጋ ሲታደግ የምናየው የኦሮሞን ህዝብ ድምጽ ያላንዳች ጠንካራ የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ ተሳትፎ ራሱ ጠቅልሎት የያዘው ኦፒዲኦ ነው።
የወያኔ መንግስት እነዚህን ሁለት ኣበይት ጥቅሞቹን ለማስጠበቅ ሲል ኦሮሞን ኣስፈራርቶ በኣገዛዙ ስር ለማስቀጠል ደፋ ቀና ይላል። ከህዝቡ መሃል የታጠቁ ወገኖችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ከጎሮቤቶቹ ህዝቦች ጋር ማጋጨት፣ ኦነግን ትደግፋለህ እያለው መዝረፍና ማሰር፣ ከዚህም ኣልፎ መግደል ላለፉት 22 ኣመታት ዋነኞቹ የስርኣቱ ተግባሮች ነበሩ። በማንኛውም መልኩ የኦሮሞ ህዝብ ክንድ ጠንክሮ ስጋት ላይ እንዳይጥለው ከመግታት ቦዝኖ ኣያውቅም። በቅርቡ ከምስራቅ ኦሮምያ የሚወጡ መረጃዎች የሚጠቁሙትም ይህንኑ ኣውነታ የሚመሰክር ነው። በነዚህ መረጃዎች መሰረት የወያኔ መንግስት ምእራብ ሃረርጌ ውስጥ የኦሮሞ ተወላጆችን ትጥቅ በማስፈታት ዘመቻ ተጠምዷል። የሚገርመው ደግሞ ከህዝቡ ላይ የሚፈቱት ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ሳይሆኑ ባህላዊ የልማትና የጦር መሳሪያዎች መሆኑ ነው። ኦሮሞ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ መታጠቅ ይቅርና ባህላዊ መሳሪያውን ሳይቀር እንዲፈታ እየተገደደ ነው። በተለይም ጉባ ቆሪቻ እና ገመቺስ ወረዳዎች ውስጥ የስርኣቱ ተላላኪዎች መንጫ በመባል የሚታወቀውን ባህላዊ መሳሪያ ከህዝቡ ላይ የመቀማት ዘመቻ ላይ ተሰማርተዋል። በምስራቅ ኦሮምያው ህዝባችን ዘንድ መንጫ ከበርካታ ክፍለ ዘመናት በፊት ጀምሮ የልማትና የመከላከያ መሳሪያ በመሆን የሚታወቅ ነው። ይህ ብቻም ሳይሆን መንጫ የኦሮሞ ህዝብ የባህል ቅርስም ነው። በዚህ የኦሮምያ ክፍል መንጫ የማንነት መገለጫ ባህል ኣካል በመሆን በዘፈንና በጭፈራ ወቅት ጥቅም ላይ ይውላል። በባህል ኣልባሳት ተውቦ መንጫ በመያዝ ሸጎዬ መጨፈር ከጥንት ጀምሮ የኦሮሞ ህዝብ ባህል ኣካል ነው። በተጨማሪም ቀደም ሲል እንደ ተጠቀሰው መንጫ የልማት መሳሪያም እንደመሆኑ መጠን ገጀራ፣ መጥረቢያና ማጭድ ከመሳሰሉት ቁሳቁሶች ጋር ተመሳሳይ ኣገልግሎት ይሰጣል። 

No comments:

Post a Comment